Tags

, , , , ,

ከድምጻችን ይሰማ የተወሰደ
ከፊሉ ህዝበ ሙስሊም የየካቲት 26 ቀጠሮን የትግሉን ፍሬ የምናጣጥምበት የነፃነት ቀን አድርጎ ይቆጥረው ነበር፡፡ ከፊሉ ምናልባትም ደግሞ ብዙሃኑ ስሊም ግን የትግሉ ዛፍ ገና የሚተከልበት እለት እንደሆነ በማሰብ ፍሬውን አሻግሮ የሚያልም ነበር፡፡ ‹‹ አስቀድሞ የበሰለ ፍሬ አስቀድሞ ይቆረጣል›› እንደሚሉት ብሂል የትግል ፍሬአችንም ፈጥኖ እንዳይቆረጥ ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ እየጎመራ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች በፍርሃት በተሸበበ ስሜትና የመንግስት የዜጎቹን መብት የማስከበር ኃላፊነትን በአጉል ጨለምተኝነት በመጠራጠር የትግል ፍሬአችን መጎምራቱን ይጠራጠራሉ፡፡ ለዚህ ጥርጣሬ ከንቱነት እስከ አሁን የተጎናፀፍናቸው ድርብ ድርብርብ ድሎች ማሳያ ናቸው፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ስለ አህባሽም ሆነ ስለመጅሊስ ማውራት ሳይሆን ማሰብ የተከለከለ በሚያስመስል ሁኔታ በፍርሃት የተሞላን ነበርን፤ በግል ወሬና በየፌስቡኩ ‹‹ ተገናኝቶ ጉዳያችንን የሚመክር አካል ያስፈልገናል›› እያልን ጥቂት ግለሰቦችን የምንናፍቅ ደካሞች ነበርን፤ በአወሊያ ካሳለፍናቸው ሳምንታት የመጀመሪያዎቹ 2 እና 3 ጁምዓዎች ‹‹ ጥቂት ግለሰቦች››፤ ፅንፈኞችና አክራሪዎች››፤ በተማሪዎች ጥየቄ ሽፋን የግል የፖለቲካ አቋማቸውን የሚያራምዱ››……….በሚሉ ቅፅል ስሞች በሚዲያዎች የምንታማ ነበርን፤
ዛሬስ?
አህባሽም ሆነ መጅሊስ በአደባባይ ማውገዝ ከመቻላችን በላይ አፍ በወጉ ያልፈቱ ህፃናት ሳይቀር ‹‹መጅሊስ አይወክለንም›› ማለት እስኪችሉ ድረስ ጠላታችንን እየተፋለምን ነው፡፡ አልሃምዱሊላህ!! ጥየቄአችንን ለማስመለስ ብልሃት የተሞላባቸው አካሄዶችን በመከተል ፈርተን ከተደበቅንበት ዋሻ ወጥተን ከመንግስት አካላት ጋር በመወያየት ላይ እንገኛለን፡፡ ሱመ አልሃምዱሊላህ!! ንቀው ያስናቁንን እና በራቸው ዝግ የነበሩትን የመጅሊስ አመራሮችን ለድርድር በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማንከራተት ችለናል፤ ከምንም በላይ ያለማንም ቀስቃሽ መብቱን መጠየቅ የሚችል በአንድ ጁምዓና በአንድ ቦታ መቶ ሺዎችን ማሰባሰብ ችለናል፤ ትግሉ መቼም ሊቋረጥ በማይችል መልኩ በማንኛውም ቅፅበት እና በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ሊቀጣጠል የሚያስችል ሃገር አቀፍ ህዝባዊ መሰረት መጣል ችለናል፤ በቀጣይ ምላሽ እንደምናገኝ ባንጠራጠርም መልስ ሊሰጠን የሚገባው መጅሊስ ሳይሆን መንግስት እንደሆነ ህዝበ ሙስሊሙ አምኗል፡፡ በመሆኑም የጥየቄዎቻችን መመለስ በህዝበ ሙስሊሙ እና በመንግስተ መካከል የመተማመንና የመደጋገፍ ስሜትን ሲያዳብር ጥያቄዎቻችንን ማስተባበል ደግሞ ተቃራኒ ስሜት መፍጠሩ እርግጥ ነው፡፡
በመሆኑም እነዚህና ሌሎች ድሎቻችን ለውጤት መቅረባችንን አመላካች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ የአላማችን ፅናት የሚፈተንበት፤ ለዲናችን ያለን ተቆርቋሪነት በተግባር የሚታይበት ጊዜ ከመቼውም በላይ በመቃረብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ትውልድ በዘመኑ ሃገራዊ የታሪክ ግድፈት እንዳይፈጠር ዘብ እንደሚቆም ታሪክ የሚዘክረው ስራ ሰርቶ እንደሚያልፍ መስካሪ አያሻም፡፡ ነገም በአላህ ፊት በዚህ አኩሪ ታሪክ ተወዳሽ እና ምንዳ ተከፋይ እንደሚሆን ተስፋ ሰንቋልና ወደ ኋላ የሚልበት ግዜ አልፏል፡፡ ሁሉም ሙስሊም በነፍስ ወከፍ ‹‹ እኔ እያለሁ በዲኔ ላይ ጉድለት አይታይም›› የሚል ኢስላማዊ መርህ አንግቦ ከውጤት ውጪ ወደቤቴ የሚመልሰኝ የለም ይላል፡፡ ድል ለሙስሊሞች! እኔ ደግሞ ድል እና ነጻነት ለንጹሃን የሰው ልጆች ሁሉ እላለሁ አላሁ አክበር!አላሁ አክበር!አላሁ አክበር!